Ethiopia Launched National Public Key Infrastructure-PKI

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ብሔራዊ ይፋዊ ቁልፍ መሰረተ ልማትን በይፋ አስጀመሩ

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ብሔራዊ የይፋዊ ቁልፍ መሰረተ ልማት (National Public Key Infrastructure - PKI) በይፋ አስጀመሩ፡፡

የሀገር ሉአላዊነትን  በተሟላ መልኩ ለማረጋገጥ የሳይበር ደህንነታችንን (cyber security) ማረጋገጥ ወሳኝ ነው፤ ለዚህ ደግሞ ይፋዊ ቁልፍ መሠረተ ልማት አስቻይ የሆነ ሚናን የሚጫወት እና ለኢትዮጵያ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን  ሽግግር የጀርባ አጥነት ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡ ከብሔራዊ ይፋዊ ቁልፍ መሰረተ ልማት በተጨማሪ በቅርቡ የተጀመረው የ5 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ኮደርስ ኢኒሼቲቭ (coders initiative) ፣ እንዲሁም ብሔራዊ የዲጂታል መታወቂያ (national ID) ፕሮግራም እንደ ሀገር ወደ ምናባዊው ዓለም በተሟላ መልኩ በመቀላቀል ተወዳዳሪ ለመሆን ወሳኝ ጉዳዮች ናቸው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ገልጸዋል፡፡

ብሔራዊ የይፋዊ ቁልፍ መሰረተ ልማት (National Public Key Infrastructure - PKI) በይነ-መረብን (Internet) መሰረት ያደረጉ ግንኙነቶችን ደህንነት ተአማኒነት ለማረጋገጥ አስፈላጊ የሆኑትን ዲጂታል ሰርተፍኬት (digital signature) በመስጠት፤ የመንግስት ተቋማት፣ የንግድ ድርጅቶች፣ እና ግለሰቦች መረጃዎቻቸው ከጠለፋ እና ከማጭበርበር የተጠበቁ መሆናቸውን አውቀው ዲጂታል እንቅስቃሴያቸውን በልበ ሙሉነት እንዲያከናውኑ እንደሚረዳቸው ተገልጧል። አያይዘውም ይፋዊ ቁልፍ መሰረተ ልማት የቴክኖሎጂ አቅማችንን ከማሳደግ በላይ፥ እርስ በርስ በተገናኘው አለም ውስጥ አስፈላጊ የሆኑትን ተአማኒነትን እና ተጠያቂነት ለማስፈን የሚያስችል ነው ተብሏል።

በብሔራዊ የይፋዊ ቁልፍ መሰረተ ልማት ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ፣ ም/ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ እና ሌሎች ከፍተኛ የመግስት የሥራ ሃላፊዎች የተገኙ ሲሆን፤ የመሰረተ ልማቱን አገልግሎት ጎብኝተዋል፡፡